ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ለሦስተኛ ጊዜ በሌላ ህትመት ወደ አንባብያን መመለሱን አስታወቀ
የካቲት ፴ (ሰላሳ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ተመስገን ይህን ያስታወቀው፤ <<ይህ ለአፈና እጅ የማይሰጥ የህዝብ ድምጽ ነው>> በሚል ርዕስ በፌስ ቡክ ገፁ ባሰፈረው ጽሁፍ ነው።
ቀደም ሲል ፍትህ ጋዜጣን፣ ከዚያም አዲስ ታይምስ መጽሔትን በ እግድ ምክንያት ያጣው ተመስገን ለሦስጠኛ ጊዜ በሌላ ህትመት መመለሱን ባስታወቀበት በዚሁ ጽሁፍ፤<<ለዜጎች ክብር የማይሰጠው ኢህአዴግ፣ ህዝብ በሚከፍለው ግብር መልሶ የሚያፍነው ኢህአዴግ፣ የሀይማኖት ተቋማትን ወደ ‹‹አጋር ፓርቲ››ነት እየቀየረ ያለው ኢህአዴግ፤ ፍትህ ጋዜጣን እና አዲስ ታይምስ መፅሄትን በጉልበት ከነጠቀን በኋላ፣ ለሶስተኛ ጊዜ በሌላ ጋዜጣ ተመልሰናል>>ብሏል።
አዲሷ ጋዜጣ ‹‹ልዕልና›› እንደምትባልና ከተመሰረተች ጊዜ ጀምሮ ለአንዴ ብቻ ታትማ ተቋርጣ እንደነበር የጠቀሰው ጋዜጠና ተመስገን፤ አሁን ግን የነበረባት የመንግስት ዕዳ ተከፍሎ፣ አሳታሚ ድርጅቱ በሀገሪቱ የአክሲዮን ሽያጭ ህግ መሰረት ወደ እኛ መዞሩን አበስራለሁ ብሏል።
እሱ የተሳተፈባት <<ልዕልና>>ጋዜጣ ለመጀመሪያ ጊዜ ዛሬ ቅዳሜ ለአንባቢያን እንደምትደርስም አስታውቋል።
<< ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ግን ‹‹አርብ አርብ ይሸበራል፤ …›› እንዲል ንጉስ ቴውድሮስ፣ ልዕልና ጋዜጣም የዕለት አርብ ድምፅ ሆና ትቀጥላለች፡፡>>ብሏል።
በአዲሷ ጋዜጣ ላይ ‹‹ከተዘጋው በር ጀርባ›› በሚል ርዕስ ላቀረበው ፅሁፍ መግቢያ የተጠቀመበትን መግቢያም እንደሚከተለው አስፍሮታል፦
በጽሁፉ መግቢያ፦<<…እነሆ በሶስተኛው በር ተገናኝተናልና አብዝቼ አላማርርም፡፡ ባማርርስ የት እደርሳለሁ? ማነው አገዛዙንስ ከስሶ የረታ? ደግሞስ ከመቼ ወዲህ ነው በሀገሬ መሬት ላይ ህግ የበላይ ሆኖ የሚያውቀው? ለማንኛውም የጠፋው ብርሃን በዚህ መልኩ ዳግም ይፈነጥቅ ዘንድ ስለተከፈለው ዋጋ ወይም ውጣ ውረድ ገድል የመፃፍ ፍላጎት የለኝም፡፡ ፍላጎቴ ከባልደረቦቼ ጋ በፀና መንፈስ በጀመርነው ጎዳና እንተምም ዘንድ ፤የመንግስትን አፈና አውግዛችሁ የሞራል ድጋፍ ለሰጣችሁን ኢትዮጵያውያን፤ እንዲሁም የአለም አቀፍ የፕሬስ ነፃነት ተሟጋች ተቋማት ላሳያችሁት አጋርነትና ተቆርቋሪነት፣ በሀገሬ ላይ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ይሰፍን ዘንድ ዋጋ በከፈሉና እየከፈሉ ባሉ ወንድምና እህቶቼ ስም ልባዊ ምስጋናዬን ማቅረብ ነው>>በመለት ነው ተመስገን የገለጸው።
No comments:
Post a Comment