Monday, 11 March 2013

ሰልጣኞቹ የምርጫ ቦርድ ስልጠና ገንዘብ ከማባከን ያለፈ ጥቅም የለውም አሉ


የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በየጊዜው የሚያዘጋጀው ስልጠና ስብሰባ ምንም ፋይዳ
የሌለው ነው ሲሉ አንዳንድ ከተለያየ ክልል የተውጣጡ ሰልጣኞች ለፍኖተ ነፃነት ገለፁ፡፡
አስተያየት ሰጪዎቹ “ምርጫ ቦርድ ስልጠና ስብሰባ እያለ በየጊዜው በሚዲያ
የሚያስነግረው ማስታወቂያ ለእርዳታ ልመና እንጂ ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት
ግንባታ ፋይዳ የለውም” ብለዋል፡፡ እነዚህ አስተያየት ሰጪዎች እንደሚሉት
“ከ1987 ዓ.ም ጀምሮ የተዘጋጁ ማንዋሎችና የአፈፃፀም መመሪያዎች ተመሳሳይ
ናቸው፡፡ የአካባቢ ምርጫ አስፈፃሚዎች የሚመለመሉት በየአካባቢው ካድሬዎችና
ደህንነቶች ነው፡፡ መስፈርቱ ለኢህአዴግ ታማኝና ታዛዥ መሆን ነው፡፡ ምርጫ
አድርገው ሲያጠናቅቁ ውለታ መጠየቅ ነው፡፡” ይላሉ አያይዘውም “ምርጫ ቦርድ በየምርጫ
ወቅት በየስብሰባው ጊዜ ጠርቶ የሚሰጠው ትምህርትም ስልጠናም ተመሳሳይ ነው፡፡
አዲስ ነገር የለውም በየጊዜው የሚሰበሰበውና አስር ጊዜ ማስታወቂያ የሚያስነግረው
በዲሞክራሲ ስም የሚያገኘውን ገንዘብ ለማወራረድና ምርጫ ቦርድ ስራ እየሰራ
ነው ለመባል ነው፡፡” በማለት ተችተዋል፡፡ ለፍኖተ ነፃነት ስማቸው እንዳይጠቀስ
የጠየቁት አስተያየት ሰጪዎቹ እንደሚናገሩት በየደረጃው ያሉ የምርጫ
ቦርድ አመራርና አስፈፃሚዎች በፖለቲካ እምነታቸው የኢህአዴግ አባላትና አፍቃሪ
ኢህአዴግ ናቸው፡፡ ከዝቅተኛ የመንግስት ሰራተኛነት የተገኙ ስለሆኑ በራስ
የመተማመን መንፈስ አለመኖር፣ በህግ የተሰጣቸውን ስልጣን ተግባራዊ እናደርግ
ቢሉም የአቅም ችግር አለባቸው፡፡ “አሁን ምርጫ ቦርድ እየሰራ ያለው ነፃና ፍትሐዊ
ምርጫ አለ ብሎ ስለሚያምን ሳይሆን በዚህ ዓይነት ‹ምርጫ›፣‹ምርጫ› እየተባለ አዲስ
ትውልድ እስከፈጠር ድረስ መቆት ነው” በማለት አስተያየታቸውን ደምድመዋል፡፡
በዚህ ዙሪያ የምርጫ ቦርድ የስራ ኃላፊዎች አስተያየት እንዲሰጡበት
ያደረግነው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም፡፡
source. ፍኖተ ነፃነት

No comments:

Post a Comment