Friday, 22 March 2013

ውያኔ በተዋሕዶ ሃይማኖታችን ላይ ያለማቋረጥ ያካሄደውን ጦርነት በተመለከተ በኮለምበስ ኦሃዮና አጎራባች ከተሞች ከምንገኝ የተዋሕዶ ልጆች የተሰጠ የአቋም መግለጫ


ውያኔ በተዋሕዶ ሃይማኖታችን ላይ ያለማቋረጥ ያካሄደውን ጦርነት በተመለከተ በኮለምበስ ኦሃዮና አጎራባች ከተሞች ከምንገኝ የተዋሕዶ ልጆች የተሰጠ የአቋም መግለጫ

መጋቢት 13 ቀን 2005 ዓ.ም. ( March 22, 2013 )

በስመ አብ፣ ወወልድ፣ ወመንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ፤ አሜን።

“እውነትን በግልጥ የማይናገር ሰው ሁከትን ይፈጥራል…”
መጽሐፈ ምሳሌ 10፥10
“የሐሰት ዕድሜ አጭር ነው፤ እውነት ግን ለዘላለም ትኖራለች። ”
መጽሐፈ ምሳሌ 12፥19
ሀገራችን ኢትዮጵያና ጥንታዊው ሃይማኖታችን ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ክርስትና ለረጅም ዘመናት ሳይነጣጠሉ ተቆራኝተው በአንድነት የኖሩ መሆናቸውን የታሪክ ማኅደር በሰፊው ይመሰክራል፡፡The Ethiopian Orthodox Union church
በሀገራችን አንድነት፤ በሕዝባችንም ነፃነት እንዲሁም በቅድስት ቤተክርስቲያናችንና በተዋሕዶ ሃይማኖታችን ጽናትና ጥንካሬ ላይ በተለያዩ ጊዜያት ልዩ ልዩ ፈተናዎች ቢገጥሙም፤ በቆራጥ የሃይማኖት አባቶቻችን ጽኑ አመራር፣ ተጋድሎና መስዋዕትነት የተጋረጡባቸውን መከራ እያለፉ ሃይማኖታችንን ጠብቀው፤ የሀገራችንና የሕዝባችንም አንድነትና ነፃነት ሳያስደፍሩ አቆይተውልናል፡፡
ፀረ-ኢትዮጵያዊና ፋሽስቱ ወያኔ ከሽፍትነት ወደ ገዥ ቡድንነት ተሸጋግሮ ሥልጣን ላይ ከወጣበት 21 ዓመታት ጀመሮ የጥፋት እጁን ዘርግቶ የሀገራችንን ሕልውና አደጋ ላይ ለመጣል እየተፍጨረጨረ ከሚገኝባቸው በርካታ አጀንዳዎች መካከል ከፍተኛውን እጅ የያዘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ለማጥፋት እንደሆነ ይታወቃል። ይህንን ተግባር እውን ለማድረግ ከጅምሩ ሕገ-ቤተክርስቲያን አፍርሶ፣ ሕጋዊ ፓትርያርኩን ከመንበራቸው አውርዶ ለስደት ከመዳረጉ በላይ የዘር መድልኦ ተልዕኮውን በመዘርጋት ቤተክርስቲያኒቱን በቁጥጥሩ ሥር አውሎ የታሪክ ቅርሶቿን በማጥፋት ላይ ይገኛል፡፡
ከዚህ በፊት በክርስትና ሃይማኖታችን ላይ ከደረሱት ጥፋቶች፤ ከዮዲት ጉዲት ሆነ ከግራኝ መሐመድ የመከራ ዘመን ይህ አሁን ያለንበት ወቅት አጅግ ላቅ ያለ መከራ የተጋረጠበት፤አጅግ በረቀቀ የጥፋት መረብ ውስጥ ሕዝበ ክርስቲያኑን ለማጥመድ የተንኮል ሴራ የተሸረበበት፤ ቤተክርስቲያንን ለማጥፋት በታሪካዊ ጠላቶቻችን ለዘመናት ሲጠኑ የኖሩ እቅዶችን ተግባራዊ በማድረግ ፋሽስቱ ወያኔ ፀረ-ኢትዮጵያና ፀረ-ተዋሕዶ ድርጊቱን በግልጽ እየፈጸመ ይገኛል።ለአስረጅነት ለመጥቀስ ያህል መናኞችና ባሕታውያን በጾም በፀሎት የሚኖሩባቸው ታሪካዊ ገዳሞቻችንን እንደ ዝቋላ፣ አሰቦት ወዘተ. . . የመሳሰሉት ለማጥፋት ሆን ተብሎ በእሳት ማጋየት፤ ታላቁን ዋልድባ ገዳምን በልማት ስም ይዞታውን በመቆጣጠር የቅዱሳን አባቶቻችን መካነ-መቃብር ማረስ፤ መናንያን መነኮሳት አባቶችን እያንገላቱ ማሰር፤ እንዲሁም በርከት ያሉትን ከገዳማቸው በማፈናቀል ማባረርን የመሳሰሉት ይገኙበታል።
በኮለምበስ ኦሃዮና አጎራባች ከተሞች ከምንገኝ የተዋሕዶ ልጆች የተሰጠ የአቋም መግለጫ ገጽ 2 ፀረ-ኢትዮጵያዊና ፋሽስቱ ወያኔ ኢትዮጵያን በ1983 እ.ኢትዮ.አ. ከተቆጣጠረ በኋላ የችግሩ መንስዔና የሁኔታዎች ሂደት እንዴት እንደነበሩ በአጭሩ እንመልከት፥
1. የችግሩ መንስዔ፥
ወልደ ኀጉሉ ( ለአጥፊነት የተፈጠረ ) የኢትዮጵያ ጠላት ፋሽስቱ ወያኔ ኢትዮጵያን በገዥነት በተቆጣጠረበት ጊዜ ተግባሩ አድርጎ የወሰደው 17 ዓመት በርሃ በነበረበት ወቅት ሲያውጠነጥን የቆየውን ኢትዮጵያንና የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖታችንን ለማጥፋት፤ እንዲሁም ከሃይማኖታችን ጋር ለሺህ ዓመታት ታሪካዊ ቁርኝት ያላቸው ሕዝባዊ ቅርሶቻችንን የማውደም ተልዕኮውን መወጣት ነበር። ይህንን እቅድ ለመፈጸም ይቻል ዘንድ በርሃ ሳለ ጣምራ ገጸ-ባሕሪ የተላበሱ፤ በጎሰኝነታቸው የሚታወቁ፤ ለሚያራምደው የጎሳ ፖለቲካ ምቹ የሆኑና የተዋህዶ ሃይማኖት ትምህርት የቀሰሙ ግለሰቦችን መልምሎ
አሰለጠነ።
ፋሽስቱ ወያኔ ኢትዮጵያን በአገዛዙ ሥር ሲያስገባ እነዚህን ሃሳዊ-መሢህና የበግ ለምድ የለበሱ ተኩላዎች የሃይማኖቱ መሪዎች አድርጎ ሾመ። በዚሁ መሠረት የጥፋት እጁን በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖታችን ላይ ዘረጋ። በቁጥጥር ሥር ያደረጋቸውን የብዙሃን መገናኛ አውታሮች በመጠቀም የሕገ-ቤተክርስቲያን ደንብ ተሟልቶና ተጠብቆ በሥርዓት የተመረጡትን ሕጋዊ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ ላይ የሀሰት ፕሮፓጋንዳ መንዛቱን ተያያዘው። የስውር ታጣቂ ኃይሉንም በመጠቀም አስገድዶ ከመንበራቸው አወረዳቸው። በምትካቸው የአድዋ ተወላጅና የወያኔ አባል የነበሩትን አባ ገብረመድህንን (ጳውሎስ) ሾመ።
በዚህ የተነሳ ሕገ ቀኖና ፈረሰ።ሥርዓተ ቤተክርስቲያንም ተጣሰ። ለመጀመርያ ጊዜ በሃይማኖታችን ታሪክ ውስጥ ሁለት ሲኖዶሶችና ገለልተኛ ቤተክርስቲያን ተከሰቱ። ይኸም በስደት የሚገኘው ሕጋዊው ቅዱስ ሲኖደስ፤ የወያኔ ተቀጥላ የሆነው የአዲስ አበባው ሲኖዶስ እና ከሁለቱም ሲኖዶሶች ውጭ ነን የሚል ገለልተኛ ቤተክርስቲያን።
2. የእርቀ ሰላሙ ሂደትና ፍጻሜ፥
የሕገ-ቤተክርስቲያን (ቀኖና) መጣስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን ከሦስት(3) ከፍሎ፤ ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ ሁኔታ በዘር ዙርያ ባጠነጠነ ባሕሪው ቤተክርስቲያናችንን ችግር ላይ ጣላት፤ አንድነቷም ተናጋ፤ምዕመናን ተስፋ ቆረጡ።
ይህ ጉዳይ በከፍተኛ ደረጃ ያሳሰባቸው የተዋሕዶ ልጆች ሁለቱን ሲኖዶሶች ለማስታረቅ ሁለት የሰላም ስብሰባዎች ጠርተውና አካሂደው ጉዳዩ በእንጥልጥል ላይ እንዳለ፤ እግዚአብሔር ሁኔታውን ለማመቻቸት ሲል አባ ገብረመድህንን (ጳውሎስ) ሳይታሰብ ወደ ማይቀረው ዓለም ወሰዳቸው። ይህ ሁኔታ ለሰላሙ በር ከፍቶ ታላቅ እድል ሰጠ። በሀገር ቤትና በውጭ ሀገራት ያሉት ምዕመናን የቤተክርስቲያን አንድነት ይመጣል ብለው ታላቅ ተስፋ አደረጉ። የሰላም ኮሚቴውም እርቀ-ሰላም ለማምጣት ከማንኛውም ጊዜ በላይ ተንቀሳቀሰ። ሆኖም ግን፣ ፀረ-ኢትዮጵያዊነትና ፀረ-ተዋሕዶ ሃይማኖት ግንባር-ቀደም አራማጁ ወያኔ የቆመለትን ኢትዮጵያን የማፍረስና ተዋሕዶ ሃይማኖታችንን የማጥፋት ዓላማውን ለማሳካት ሲል የሰላሙን በር ለአንዴና ለመጨራሻ ጊዜ ዘጋው።
3. ወያኔ ፓትርያርክ ስለመሰየሙ፥
ሕጋዊው ፓትርያርክ በሕይወት እያሉ፤ ወያኔ በ21 ዓመታት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ሕገ-ቤተክርስቲያን ጥሶና ለሁለተኛ ጊዜም ከራሱ ጎሳ መዞ አውጥቶ አባ ማትያስን ፓትርያርክ አድርጎ ሾመ። የቀኖናውን መጣስ የተቀበሉት፤ የሰላሙንም ሂደት የረገጡት፤ የቤተክርስቲያን አንድነት ጥሪ ወደ ጎን ገሸሽ አድርገው የጣሉት አባ ማትያስ ማን ናቸው?
ሀ/ የኢትዮጵያዊ ዜግነታቸውን ክደው የሌላ ባዕድ ሀገር ዜግነት የተጎናፀፉ፤ ይኸም በተዋሕዶ ሃይማኖታችን አንጻር እንደ አንድ ታላቅ ሕጸጽ የሚታይ ነው።
ለ/ በደርግ ዘመነ መንግሥት ጊዜ በእየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት ጳጳስ በነበሩበት ወቅት፤ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በመገንጠል ቤተክርስቲያንን ከሁለት በመክፈላቸው፤ በወቅቱ የነበሩት 3ኛ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለሃይማኖት ውግዝ ከመአርዮስ ብለው ጵጵስናቸውን ገፈዋቸዋል። በዚያን ወቅት፣ በስደት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ክደው አፖስቶሊክ ቤተክርስቲያን (Apostolic Church) ያቋቋሙት አባ ጳውሎስ ቀደም ሲል በስውር የተደራጁበት የወያኔ ድርጅት ለሥልጣን ሲበቃ ፓትርያርክ አድርጎ ሾማቸው። አባ ገብረመድህንም ዘር ከልጓም ይስባል እንዲሉ በጎሳ ወንድማቸውን አባ ማትያስ ላይ የተጣለውን ውግዘት በመተላለፍ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሊቃውንት ጉባዔ ሳያውቀው ሥልጣናቸውን መከታ በማድረግ በግለሰብ ደረጃ እንደ ችሮታ የጵጵስና ሥልጣናቸውን መልሰዋል። ይኸም ከፍተኛ የሆነ የሕገ-ቤተክርስቲያን ጥሰት ነው።
ፀረ-ኢትዮጵያዊና ፋሽስቱ ወያኔ ቡድንና ታሪካዊ ጠላቶቻችን በጣምራ በማበር በኢትዮጵያዊነት፣ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖታችንና በሃይማኖታዊ ቅርሶቻችን ላይ ያወጁብንን መጠነ ሰፊ ጦርነት በሰፊው ከገመገምን በኋላና ከላይ የተጠቀሱትን እውን ታሪካዊ ክስተቶች በማገናዘብና በማጤን ፤ የሚከተለውን የአቋም መግለጫ አውጥተናል።
4. የአቋም መግለጫ፥
1ኛ/ ለ2ሺህ ዓመታት ቅዱሳንና ብፁዓን አባቶቻችን ካወረሱን ሕገ-ቤተክርስቲያን አኳያ፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሕጋዊ ቅዱስ ሲኖዶስ በስደት የሚገኘውና በ4ኛው ፓትርያርክ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ የሚመራው መሆኑንና በኢትዮጵያና ከኢትዮጵያ ውጭ በዓለም ላይ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ቅዱስነታቸው አባት መሆናቸውን እናምናለን፣ እንገልጻለን።
2ኛ/ ሕገ-ቤተክርስቲያንን በመጣስ ወያኔ የሾማቸውን ፓትርያርክ ተብዬ አባ ማትያስን በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን አባትነታቸውን እንዳይቀበሉ በስደት የሚገኘው ሕጋዊው ቅዱስ ሲኖዶስ ባለፈው ጥር 2005 ዓ.ም. በሎስ አንጀለስ ከተማ፣ ካሊፎርኒያ፣ አሜሪካ ባካሄደው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ ላይ ያስተላለፈውን የውግዘት መግልጫ እንደግፋለን፣ እንቀበላለን። እውነተኛ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እምነት ተከታዮች የሆኑ ሁሉ ይህን ውሳኔ እንዲቀበሉ ጥሪ እናስተላልፋለን።
3ኛ/ በአሁኑ ጊዜ የተዋሕዶ ሃይማኖታችንና የቤተክርስቲያናችን ሕልውና በከፍተኛ አደጋ ላይ ይገኛል። ስለዚህ፣ ገለልተኛ ቤተክርስቲያን ነን የምትሉ ለተዋሕዶ ሃይማኖታችን ፅናት፤ ለቤተክርስቲያናችን አንድነትና ወያኔ የፈጠረብንን አደጋ ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት እንዲሁም በ4ኛው ፓትርያርክ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ላይ ወያኔ የፈጸምው ግፍና በደል በተለያዩ ማስረጃዎች የተረጋገጡ ስለሆኑ፤ 21 ዓመታት ከተጓዛችሁበት መንገድ ወጥታችሁ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ አባትነት ተቀብላችሁ ቅዱስነታቸው የሚመሩት በስደት የሚገኘውን ሕጋዊው ቅዱስ ሲኖዶስ ተከታይ እንድትሆኑ ኢትዮጵያዊና ክርስቲያናዊ ጥሪያችንን እናቀርባለን። በጥብቅ ማሳሰብ የምንፈልገው ከሕገ-ቤተክርስቲያን አንጻር ገለልተኝነት የሚባል ነገር የለም። በእኛ እምነት 21 ዓምት ሥርዓተ-አልበኝነትን ያስፋፋው የገለልተኛ ቤተክርስቲያን በር ተዘግቷል።ምርጫው፥ ለተዋሕዶ ሃይማኖታችንና ለቤተክርስቲያናችን አንድነት ከቆመው በስደት ከሚገኘው ሕጋዊ ቅዱስ ሲኖዶስ ጋር ወይም ታሪክና ሕዝበ-ክርስቲያኑ ከሚፋረደው ወያኔ በአምሳሉ ከቀረጸው የአዲስ አበባው ሲኖዶስ ጋር መሆን ብቻ ነው።
4ኛ/ ፀረ-ኢትዮጵያዊና ፋሽስቱ ወያኔ 21 ዓመታት በተከታታይ በኢትዮጵያ ሕዝብ ጀርባ ላይ የሚፈጽመው ግፍና ሰቆቃ አልበቃው ብሎት፤ ኢትዮጵያዊ ዜግነታችንን (ተወላጅነታችንን) እና ከደማችን ውስጥ ያለውን ተዋሕዶ ሃይማኖታችንን ለመንጠቅ “ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን’’ የሚለውን ስም መጠቀም አትችሉም በማለት በውጭ ሀገራት ያቋቋምናቸውን አብያተ-ቤተክርስትያናት ከቻለ ለመንጠቅ ካልሆነ ለማፍረስ በሕገ-ወጡ ፓትርያርክ አባ ማትያስ አስተባባሪነት ክስ እንመሰርታለን በሚል የጀመረውን የማስፈራራት ዘመቻ በጥብቅ እናወግዛለን፤ በህብረት እንቋቋመዋለን።
5ኛ/ በውጭው ዓለም ያለውን ሕዝበ-ክርስቲያን ለማሰባሰብና ለማስተባበር እንዲያመች ይረዳ ዘንድ፤ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ የሚመራው ቅዱስ ሲኖዶስ ጊዜና ቦታ መርጦ፤ ጳጳሳት፣ ካህናት፣ ዲያቆናት፣ መዘምራንና የምዕመናን ተወካዮችን ያካተተ ሁሉን-አቀፍ “ የተዋሕዶ አንድነት’’ መንፈሳዊ ጉባዔ እንዲጠራ እንጠይቃለን።
6ኛ/ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ መሪነት፤ ብፁዓን አባቶችን፣ አበው ካህናትን፣ ወንድም ዲያቆናትን፣ መዘምራንን፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ምዕመናንና የኢትዮጵያ እስልምና ሃይማኖት ተከታዮችን ያቀፈ በዋሽንግተን ዲሲና በተለያዩ አህጉራት በሚገኙ ታላላቅ ከተማዎች በአንድ ቀን የሚካሄድ ዓለም-አቀፍ “ኢትዮጵያንና ሃይማኖቷን አድን’’ “ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ ቅዱስ ሲኖዶሱ አመች ቀንና ሰዓት መርጦ እንዲጠራ እንጠይቃለን።
ወስብሃት ለእግዚአብሔር።
ኃያሉ ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ተዋሕዶ ሃይማኖታችንን ይታደግ!
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!

No comments:

Post a Comment