- መንግሥት ሙስናን ለመቀነስ የባለስልጣናትን ንብረት እንደመዘገበ ሁላ ቤተክርስቲያኒቱ የጳጳሳቱን ንብረት መመዝገብ ይኖርባታል፡፡
- እስከ አሁን ብዙ ንብረት በመያዝና በማስቀመጥ ክስ ያልተሰማባቸው አባት አቡነ ጳውሎስ ናቸው፡፡
- ታምራት ላይኔ ጥገኝነት ለመጠየቅ ተናገረ የተባለውን ነገር እንደ ታሪካዊ ማስረጃ ለመውሰድ በግሌ እቸገራለሁ፡፡ ይህንን ካደረገ ቤተክርስቲያኒቱን ይቅርታ መጠየቅና ለተፈጠረው ቀውስም ሃላፊነት መውሰድ ይኖርበታል፡፡
- የ6ኛ ፓትርያርክ ምርጫው ከመንፈሳዊነት ወጣ ባለ መልኩ የምረጡኝ አይነት የምርጫ ቅስቀሳዎች ነበሩ፡፡
- እሳት በተነሳ ቁጥር ቦታህን እየለቀክ ከተሰደድክ ለችግሩ መፍትሄ መስጠት አትችልም፡፡
- እርቀ ሰላሙ እንዲጀመር መንገድ የጠረጉት አቡነ ማትያስ ናቸው ፤ አቡነ ጳውሎስንና አቡነ መርቆሪዎስን ብቻቸውን ለማገናኝት እቅድ ነበራቸው ፡፡
ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ከወቅቱ የቤተክርስቲያን ጉዳይን በሚመለከት ከላይፍ መጽሄት የመጋቢት ወር እትም ቁጥር 102 ጋር አጭር ቆይታ አድርጎ ነበር ፡፡ ዲያቆን ዳንኤል ቆይታው ይህን ይመስላል…. ያንብቡት
ላይፍ፡- የፓትርያርኩ ምርጫ ለማከናወን 800 ሰዎች ድምጽ እንዲሰጡ መደረጋቸው አይዘነጋም፡፡ እነዚህ ሰዎች እንዴት ተመረጡ ? አንተስ ከመራጮቹ አንዱ ነበርክ ?
ዲ/ን ዳንኤል፡- የተደረገው ነገር መራጮች በአገሪቱ ካሉት ሀገረ ስብከቶች እንዲመጡ ነው፡፡ እኔ ከመራጮቹ አንዱ አልነበርኩም፡፡ ምክንያቱም ብዙም ደስተኛ አልነበርኩም፡፡ ፍላጎቴ ሂደቱን መታዘብ እንጂ መራጭ መሆን አልነበረም፡፡ ሂደቱ ውስጥ በመግባት አንተ ራስህ አካል ስትሆን ምርጫውን በደንብ ለመመልከት አትችልም፡፡ የምርጫ ሂደቱ በጎም ይን መጥፎ ነገሮች የተስተዋሉበት ነበር፡፡ በተለይ ከሂደቱ በፊት የነበሩ ነገሮች ደስ የማይሉ ነበሩ፡፡ ከመንፈሳዊነት ወጣ ባለ መልኩ የምረጡኝ አይነት የምርጫ ቅስቀሳዎች ነበሩ፡፡ በነገራችን ላይ በአንድ ወይም በሁለት አባቶች ላይ ሳይሆን ከዚያም ከፍ ባሉት ከዘር ጋር በተገናኝ የቡድንተኝነት እንቅስቃሴ ነበር፡፡ ከዚህ ውጪ መንግስት እንዲህ ብሏል የሚሉ ነገሮች መደመጣቸው ሂደቱ ላይ ጥላ አጥልተውበት ነበር፡፡ ችግሩ የተፈጠረው አድራጊዎቹ እንዲህ ለማድረግ በመፈለጋቸው ብቻ ሳይሆን ሕጉም ክፍተት ስለነበረው ነው፡፡ ለምሳሌ ለምርጫ ድምጽ እንዲሰጡ የተመረጡ ሰዎች ከአንድ ሀገረ ስብከት 13 መሆናቸው እንጂ እነዚህ ሰዎች እንዴት እንደሚመረጡ ሕጉ አይገልጽም፡፡ ስለዚህ ሊቀ ጳጳሳቱ የፈለጉትን ሰው እንዲመርጡ እድል ይሰጣቸዋል ማለት ነው፡፡ እኔ ሌሎች አገሮች ላይ አምስቱንም ኦሪየንታል ቤተ ክርስቲያናት አይቻለሁ፡፡ እነርሱ ጋር አጥቢያዎች በወረዳ ደረጃ ተሰብስበው የሚወክላቸውን መራጭ ይመርጣሉ፡፡ ውክልና የሚመጣው ከታች ወደ ላይ ነው፡፡ ደግሞም ለአንድ አገረ ስብከት 13 ሰው መባል የለበትም ፡፡ ድሬደዋ እና መቀሌ እንደገና ምዕራብና ምስራቅ ጎጃም ፤ ሰሜን ሸዋን እኩል ማድረግ አይቻልም፡ ድሬደዋ እና መቀሌ ያሉት አንድ አንድ አገረ ስብከቶች ናቸው፡፡ ስለዚህም ሁሉንም በአንድ በመጨፍለቅ በ13 ሰው እንዲወከሉ ማድረግ ትክክል አይደለም፡፡ ሌላው ለፓትርያርክነት በእጩነት የሚቀርበው አባት ያለው ስብዕና በእኛ ሁኔታ የሚመዘንበት መንገድ የለም፡፡ግብጽን ብንወስድ ለምርጫ የሚቀርቡት አባቶች በመጀመሪያ በፖሊስ አሻራቸው እንዲመረመር ይደረጋል፡፡ በዚህም ሰውየው ወንጀል ሰርቶ መሆኑንና አለመሆኑን እንዲጣራ ይደረጋል፡፡ ምክንያቱም ፓትርያርክ ከሆነ በኋላ ከስልጣኑ ስለማይወርድ ማጣራት ይደረጋል፡፡ እነዚህን ነገሮች የሚያደርጉት ጥሩ አባት ለማግኝት ጭምር ነው፡፡
ላይፍ፡- ቤተክርስቲያኒቱ ፓትርያርኳን ለመሾም ምርጫ ውስጥ መግባቷን እንዴት ትመለከተዋለህ ?
ዲ/ን ዳንኤል፡- ምርጫ ውስጥ መግባቷ ወንጀል አይደለም ፡፡ በእርግጥ አለማዊ ባለመሆኑ መንፈሳዊነትን መላበስ ነበረበት፡፡ ነገር ግን ምረጡኝ በማለት የቀሰቀሱ አባቶች የነበሩትን ያህል እኮ ከእኔ ይልቅ ሌሎች ቢመረጡ ይሻላል ያሉም ነበሩ፡፡ ከዚህ ቀደም አባት ይሁኑን ተብለው ከገዳም ታስረው የመጡ አባቶች ነበሩ፡፡ እንዲህ አይነት ታሪክ የነበራት ቤተክርስቲያን እዚህ ደረጃ መድረሷ ያሳዝናል፡፡ በእኔ እምነት ትልቁ ችግር የነበሩት ምርጫ ላይ የቀረቡት አባቶች ሳይሆኑ በእነርሱ ዙሪያ ተሰብስበው ነገ እንጠቀም ይሆናል ያሉ ሰዎች ናቸው፡፡ ብዙ ርቀት ሄደው አከሌን ምረጡ ሲሉ የነበሩ ሰዎች እነዚህ ናቸው፡፡
ላይፍ፡- የፓትርያርኩ ሹመት ከምርጫ ካርድ የመነጨ መሆኑ መንፈሳዊነቱን አያደበዝዘውም ?
ዲ/ን ዳንኤል፡- ሰዎች ከምርጫ ካርድ ይልቅ በዕጣ ቢሆን መንፈሳዊነትን ይላበስ ነበር በማለት ያስባሉ፡፡ ነገር ግን ለቤተክርስቲያናችን አባቶችን በምርጫ መሾም አዲስ ነገር አይደለም፡፡ የኦሪየንታል አብያተክርስቲያናት ልምድ ከተመለከትን የምናገኝው ሁለት ነገር ነው፡፡ ግብጾች በእጣ ያምናሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ አባቶቻውን በካርድ ይመርጣሉ፡፡ በቤተክርስቲያናችን ታሪክ ፓትርያርክን በካርድ መምረጥ የተጀመረው ከአቡነ ተክለሃይማኖት ጀምሮ ነው፡፡ከድምጽ ውጪ የተመረጡ አባቶች አቡነ ባስልዮስና አቡነ ቴዎፍሎስ ናቸው፡፡ የእጣውም ይሁን የድምጹ ትክክለኛ መስመር ይዘው እስከተከናወኑ ድረስ ስህተት አይሆኑም፡፡
ላይፍ፡- በምርጫው ሂደት አሸናፊ ሆነው የወጡት አባት ምርጫው ከመከናወኑ አስቀድሞ የፓትርያርክነቱን መንበሩን እንደሚይዙ ይነገርባቸው ከነበሩ አባት ከመሆናቸው አንጻር የምርጫ ሂደቱን አጠያያቂ አያደርገውም?
ዲ/ን ዳንኤል፡- ምርጫው ግልጽ ነበር አልነበረም? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ በምርጫው ሂደት ተሳታፊ የነበሩ ሰዎች የሚሰጡትን ምላሽ መጠበቅ አስፈላጊ ነው፡፡ የተጠበቀው ውጤት ብቻ መምጣቱ ምርጫው ነጻ አልነበረም አያሰኝውም፡፡ አቡነ ማትያስ ከኋላ የነበራቸውን ታሪክ መለስ ብለን ከተመለከትን ይህንን ለማለት የሚያስችል ነገር አናገኝም፡፡ ነገር ግን ሂደቱን ካየን አስገራሚ ነገር እናገኛለን፡፡ አቡነ ጳውሎስ በቤተክህት ፖለቲካ ውስጥ ወይም ቅራኔ የነበራቸው ሰው አለመሆናቸው በምርጫው ማሸነፍ ችለዋል፡፡ እነዚህ ነገሮችን ስታይ ከቤተክህነቱ ራቅ ብሎ የቆየ አባት የመመረጥ እድሉ ሰፊ መሆኑን ትመለከታለህ፡፡ አቡነ ማትያስም እንደ አቡነ ጳውሎስ አብዛኛውን ጊዜያቸውን ያሳለፉት በውጭ ሀገር ነው፡፡ በፓትርያርክነት ቦታ ተገምተው የነበሩ ብቸኛ አባት አቡነ ማትያስ ብቻ አልነበሩም፡፡ እንዲያው የሚበዙት ጠብቀው የነበሩት ሌሎችን ነው፡፡
ላይፍ፡- አቡነ ማትያስ ወደ አሜሪካ ካቀኑ በኋላ ዜግነታቸውን መለወጣቸው ይታወቃል፡፡ አንድ አባት የግል ጥቅሙን በማሰብ ዜግነቱን እስከመቀየር ከደረሰ በኋላ ዜግነቱን የጣለበት ሀገር በፓትርያርክነት እንዲመራ ተመረጠ መባሉ እንግዳ ነገር አይሆንም ? የቤተክርስቲያኒቱ ሕግ በዚህ ዙሪያ ምን ይላል ?
ዲ/ን ዳንኤል፡- ዜግነትን በተመለከተ የቤተክርስቲያን ሕግ የሚለው ነገር አለ፡፡ ለእኔ የቤተክርስቲያኒቱ አባት ዜግነት የፈለገው መሆኑ ጽድቅ ወይም ሃጥያት አይደለም፡፡ በደብረ ሊባኖስ ታሪክ ወእጨጌ ከተባሉ ጳጳሳት ከግብጽ በመለጠቅ ገዳሙን ይመራ የነበረው አቡነ እምባቆም የመናዊ ነበር፡፡ አቡነ ማትያስ ምርጫው ከመድረሱ በፊት አቡነ ጳውሎስ በህይወት እያሉ አሜሪካዊ ዜግነታቸውን መመለሳቸውን ተናግረዋል፡፡ ሌሎች ሰዎች ደግሞ ዜግነታቸውን አልመለሱም ይላሉ፡፡ እነዚህ ነገሮች በማስረጃ ቀርበው እስካላየን ድረስ ለመፍረድ እንቸገራለን፡፡
ላይፍ፡- አቡኑ መለስኩ ማለታቸው በራሱ ኢትዮጵያዊነትን በመተው የአሜሪካ ዜግነት ለማግኝታቸው ማረጋገጫ ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት አቡኑ ላይ ትችት ለሚሰነዝሩ ወገኖች ነገሩ በር አይከፍትም?
ዲ/ን ዳንኤል፡- ሰማያዊና ምድራዊ ዜግነት ይለያያል፡፡ ለቤተክርስቲያን መሪነት የሚያስፈልገው መንፈሳዊነት ነው፡፡ በግሌ ዜግነቱ ምንም ቢሆን ልዩነት አይፈጥርም፡፡ በጣም ብዙ አባቶች በፖለቲካም ይሆን በኢኮኖሚ ጫና ወደ አሜሪካ ሄደዋል ፤ እነዚህ አባቶች በዚያ የተሻለ ነገር ለማግኝት ሲሉ በሁኔታዎች አስገዳችነት ዜግነታቸውን ይቀይራሉ፡፡ እንዲህ መሆኑ በቤተክርስቲያኒቱ እስከ አሁን ድረስ እንደ ችግር አልታየም፡፡
ላይፍ፡- ከምርጫው በፊት አሜሪካ የሚገኝው ሲኖዶስ ጋር እርቅ ለማውረድ እንቅስቃሴ ተጀምሮ ነበር ፤ በግልጽ የእርቁ ደጋፊ ነበር ?
ዲ/ን ዳንኤል፡- እርቅ እደግፋለሁ፡፡ ሁለቱ አባቶች በአንድነት ሆነው ስድስተኛውን ፓትርያርክ ቢመርጡ ደስ ይለኝ ነበር፡፡ ነገር ግን መርቆሪዎስ በህይወት እስካሉ ድረስ ሌላ አባት መምረጥ አይገባውም ከተባለ ግን ከሶስት ነገር አንጻር አያስኬድም፡፡ አንደኛ በትክክል በእኒህ አባት መፍረድ ከባድ ቢሆንም መንበሩን ትተው ሄደዋል፡፡ ወደ መንበሬ መልሰኝ በማለት ሲጸልይ የነበረ አባት ሳይሆኑ በ1985 ዓ.ም በሜሪላንድ ሕግ የተመዘገበ የኢትዮጵያ ሲኖዶስ የተመሰረተበት ሕግ ከአምስቱ ኦሪየንታል አብያተ ክርስቲያናት የሚቆጠር ስድስተኛ ቤተክርስቲያን ለመመስረት እንደሆነ በግልጽ ይናገራል፡፡ ስለዚህ ጥያቄው ወደ መንበር የመመለስ ብቻ አይደለም፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ባለፉት 20 ዓመታት ይችን ቤተክርስቲያን ወደድንም ጠላንም ፓትርያርክ ሾማ ሕይወት ቀጥላለች፡፡ ጥፋት ጠፍቷል የሚሉ ሰዎች ወደ ኋላ መመለስ አለብን እያሉ ነው፡፡ ነገር ግን ሁል ጊዜ የተሰደደ ሰው ብቻ እንደ ጀግና ለምን እንደሚቆጠር አይገባኝም፡፡ ጀግና ሀገር ውስጥ ያለውን መከራ የተቋቋመ ወይስ ጥሎ የተሰደደ ሰው ነው? ችግርና ጥፋቱ የጋራ ነው መባል የነበረበት እናንተ አጥፍታችኋልና እኛን ወደ ቦታችን መልሱን ሳይሆን ሁላችንም አጥፍተናል ከአሁን በኋላ ለዚች ቤተክርስቲያን ሲባል በጋራ ምን እናድርግ ? ነበር ማለት የነበረባቸው ፡፡ እርቁ የተጀመረው በአቡነ ጳውሎስ ዘመን ነው፡፡ በእሳቸው ጊዜ እርቁ ተፈጽሞ ቢሆን ኖሮ ምን ሊኮን ነበር? ለምንድነው የአንድን ሰው ሞት እንደ መልካም አጋጣሚ የምንቆጥረው ? የሞቱት እኮ በመቅሰፍት አይደለም፡፡ የቫቲካኖች መሪ ስልጣን አልፈልግም እናንተ ተስማምታችሁ ስሩ በማለት መንበራቸውን ተሰናብተዋል፡፡ እኔ ከመጀመሪያ የነበረኝ አቋም እርቁ እንዲፈጸምና በተቻለ ፍጥነት ተተኪው ፓትርያርክ እንዲመረጥ ነበር፡፡ አቡነ መርቆሪዎስ ከአሁን በኋላ አልሰራም በማለት ለሲኖዶስ ደብዳቤ አስገብተው ነበር፡፡ ስለዚህ ቦታውን ለመልቀቃቸው ማረጋገጫ ነው፡፡ በፓትርያትክ ላይ ፓትርያርክ ተሾመ በማለት አቡነ ጳውሎስን መውቀስ ከብዙ ነገር አንጻር ተገቢ አይደለም፡፡ አቡነ ጳውሎስ በሰሩት ስራ ትክክል ነበሩ? ወይም አልነበሩም? ማለት ሌላ ነገር ነው፡፡ ነገር ግን ቀኖናዊ ነበሩ፡፡
ላይፍ፡- የአሜሪካው ሲኖዶስ ወይም አቡነ መርቆሪዎስ ባወጧቸው መግለጫዎች ጥያቄያቸው የፓትርያርክነት መንበር ይሰጠን ሳይሆን እርቅን ማስቀደም እንደሆነ ደጋግመው ገልጸዋል፡፡
ዲ/ን ዳንኤል፡- ጥያቄያቸው አንድና አንድ ነው፡፡ ወደ መንበራችን እንመለስ የሚል፡፡ ያወጧቸው መግለጫዎች በእጄ ላይ የሚገኙ በመሆናቸው ይህንኑ ማሳየት እችላለሁ፡፡
ላይፍ፡- አቡነ መርቆሪዎስ በፖለቲካ ጫና አገር ጥለው ለመሰደዳቸው በእሳው ወገን ያሉ ሰዎች ከሚሰጡት መግለጫ በተጨማሪ በቅርብ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ታምራት ላይኔና ፕሬዝዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ አቡኑ በፖለቲካ ጫና መንበራቸውን ስለመልቀቃቸው ተናግረዋል፡፡ አንተ ደግሞ ከአሁን በኋላ አልሰራም ማለታውን ግላዊ ታደርገዋለህ፡፡
ዲ/ን ዳንኤል፡- ታምራት ላይኔ ይህን ተናግረዋል በማለት የምቀበለው በትክክል እዚህ ተገኝቶ በይፋ ይህንን አድርጌአለሁ በማለት 40 ሚሊየኑን የቤተክርስቲያኒቱን አማኝ ይቅርታ ሲጠይቅ ነው ፤ ጥገኝነት ለመጠየቅ ተናገረ የተባለውን ነገር እንደ ታሪካዊ ማስረጃ ለመውሰድ በግሌ እቸገራለሁ፡፡ ይህንን ካደረገ ቤተክርስቲያኒቱን ይቅርታ መጠየቅና ለተፈጠረው ቀውስም ሃላፊነት መውሰድ ይኖርበታል፡፡ ቤተክርስቲያን ከፖለቲካው ጫና ነጻ ሆና አታውቅም፡፡ አሁንም ይሁን ከዚህ በፊት ጫናዎች ነበሩ፡፡ የቤተክርስቲያኒቱ አባቶች ጫናውን በመቋቋም እዚህ ደርሰዋል፡፡እሳት በተነሳ ቁጥር ቦታህን እየለቀክ ከተሰደድክ ለችግሩ መፍትሄ መፍጠር አትችልም፡፡ ዋልድባን መርዳት የማይችል ሲኖዶስ አሜሪካ ውስጥ መፈጠሩ ምንም አይጠቅምም፡፡
ላይፍ፡- በሁለቱ ሲኖዶሶች መካከል ተጀምሮ የነበረው እርቅ የተቋረጠው የአሜሪካው ስልጣን በመጠየቁ ሳይሆን የመንግሥት ፍላጎት ባለመሆኑ ነው የሚሉ ብዙ ሰዎች ናቸው፡፡ የቀድሞ የሕወሓት አመራር አቶ ስብሃት ነጋ ለላይፍ መጽሄት በሰጡት ቃለ ምልልስ ይህንኑ በማንጸባረቅ “ለእርቅ ቄሶቹን የላኩ ሰዎች መሰቀል ይኖርባቸዋል” ብለዋል፡፡ ይህንን እንዴት ትመዝነዋለህ?
ዲ/ን ዳንኤል፡- አቦይ ስብሃት የተናገሩት የመንግሥት አቋም በማድረግ ለመውሰድ እቸገራለሁ፡፡ ምክንያቱም አሁን እሳቸው በመንግሥት ስልጣን ላይ አይገኙም፡፡ እኔ የምወስደው የግላቸው አቋም በማድረግ ነው፡፡ የግላቸው አቋም ቢሆንም ትክክል ነው ብዬ አልወስደውም፡፡ ከሃይማኖትም ከሕግም አንጻር ንግግራቸው ትክክል አይደለም፡፡ ለእርቅ የሄደ ሰው በሕግ ይሰቀል አይባልም፡፡ የደርግ ባለሥልጣናት እንኳን ከእስር ቤት እንዲወጡ ያደረገች አገር ለእርቅ የተነሳሱ ሽማግሌዎችን ትሰቅላለች የሚል እምነት የለኝም፡፡ በሃይማኖትም“የሚያስታርቁ ብጹአን ናቸው” ነው የሚባለው፡፡ ለእርቅ የሄዱ ሰዎች ይመሰገኑ ይሆናል እንጂ አይወገዙም፡፡ እርቅ ሂደት ውስጥ ስህተት ሊኖር ይችላል፡፡ እኔም የማልቀበላቸው ነገሮች አሉ፡፡ በነገራችን ላይ የእርቁን ሂደት የጀመሩት አሁን የተሸሙት አቡነ ማትያስ ናቸው ፡፡ ይህን ስለተሾሙ ብቻ የምናገረው አይደለም፡፡ አሜሪካ በሄድኩ ጊዜ አግኝቻቸው ብዙ ዶክመንቶችን ሰጥተውኛል፡፡ ማንም ባላሰበበት ወቅት እዚህ ድረስ በመምጣት ሲኖዶስ እርቅ እንዲፈጽም ተማጽነዋል፡፡ ከ10 ዓመታት በፊት ደብዳቤ በመጻፍ እርቅ እንዲወርድ ሲማጸኑ ነበር፡፡ እንዲያውም አቡነ መርቆሪዎስንና አቡነ ጳውሎስን ብቻቸውን የማገናኝት እቅድ ነበራቸው፡፡ ይህ ያልተሳካው አንድ አንድ አቡነ መርቆሪዎስን ይቀርቡ የነበሩ አባት እንዴት እኔ ሳልሰማ ይህ ይሆናል? በማለት አቡነ መርቆሪዎስ እንዳይሄዱ በማገታቸው ነው፡፡ ሁለቱ አባቶች ኒውዮርክ ላይ ለመገናኝት ፈቃደኞች ሆነው ነበር፡፡ ሁለቱ አባቶች ተገናኝተው ተያይተው አያውቁም፡፡ ምክንያቱም አቡነ ጳውሎስ በቦሌ ሲገቡ አቡነ መርቆሪዎስ በሞያሌ በኩል ወጥተዋል፡፡ ብዙ ጥረቶች ተደርገዋል፡፡ አቡነ ጳውሎስ ካረፉ በኋላ ሰዎች አቡነ መርቆሪዎስን በማምጣት ችግሩ እንዲፈታ አስበው ነበር፡፡
ላይፍ፡- አሁን እርቁን ሲመኙ የነበሩት አባት ወደ መንበሩ በመምጣታቸው በቀጣዩ የተቋረጠው እርቅ ድርድር ቀጥሎ ሁለቱ ሲኖዶሶች አንድ ይሆናሉ ብለህ ተስፋ ታደርጋለህ?
ዲ/ን ዳንኤል፡- እኔ በጣም ተስፈኛ ነኝ ፡፡ እርቁ ጥሩ የሚሆነው መንበሩ ላይ ፓትያርክ ከተቀመጠ በኋላ ነው፡፡ ፓትርያርኩ ካለ እኔን አስቀምጡኝ? የሚል ጥያቄ ስለማይነሳ ይሳካል የሚል እምነት አለኝ፡፡
ላይፍ፡- በአቡነ ጳውሎስ ስም የተመዘገቡ ንብረቶች አዲሱ ፓትርያርክ ወይም ቅዱስ ሲኖዶስ በይፋ ለህዝብ በመግለጽ ገቢ ያደርጋቸዋል ብለህ ታስባለህ? ከሃብታም ነጋዴዎች ያልተናነሰ ሀብት ያካበቱ ጳጳሳት እንዳሉም እየሰማን ነው?
ዲ/ን ዳንኤል፡- ወደ ግብጽ በሄድኩበት ሰዓት ከተማ ውስጥ ያገኝኋቸው ሁለት መነኮሳትን ብቻ ነበር፡፡ እነዚህም መነኮሳት ኢትዮጵያውያን ነበሩ፡፡ ሌሎች መነኮሳት የሚቀመጡት በገዳም ነው፡፡ በዋልድባ ስንት መነኩሴ አለ ? በአራት ኪሎስ ? ለከተማ የቀረቡ መነኮሳት ደግሞ በከተማ ስርዓት መጠመዳቸው አይቀሬ ይሆናል፡፡ ቤተክርስቲያን ጳጳሳቱ ምን ያህል ንብረት እንዳላቸው የምታውቅበት መንገድ የላትም፡፡ ቤተክርስቲያን ሲሆን ለመንግሥት አርዓያ መሆን ይገባት ነበር፡፡ ይህ ባለመሆኑ ከመንግሥት ልትማር ይገባል፡፡ መንግሥት ሙስናን ለመቀነስ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ሀብት እመዘግባለሁ ብሏል፡፡ ስለዚህም ቤተ ክርስቲያን ይህን ማድረግ ይኖርባታል፡፡ ገዳሞቻችን በመነኩሴ እጥረት እየተራቆቱ ነው፡፡ እኔ ከላይ ብቻ ሳይሆን ከታች መሰራት እንዳለበት ይሰማኛል፡፡ እስከ አሁን ድረስ ጳጳሳቱ ንብረት አፍርተው ይሆናል፡፡ ከአሁን በኋላ ግን እንዲህ አይነት ንብረት ነበረኝ ለቤተክርስቲያኒቱ ሰጥቻለሁ ማለት መጀመር መቻል አለባቸው፡፡ የቤተክህነቱን ጸባይ ሳውቅ ግን እንዲህ አይነት ነገር ይፈጠራል ለማለት እቸገራለሁ፡፡ ንብረት በመያዝና በማስቀመጥ ረገድ እሰከ አሁን ብዙ ያልተሰማባቸው አባት አቡነ ጳውሎስ ናቸው፡፡ ምናልባት ዘመዶቻቸው ረድተው ይሆናል ካልተባለ በቀር ብዙ ንብረት የላቸውም፡፡
ዲ/ን ዳንኤል ካደረገው ቃለ መጠይቅ እኛን ይመለከታል ያልነውን ብቻ ወስደናል ፤ የተቀረው ቃለ መጠይቅ የጊዜው እጉርጎሮ የሆነው የፕሮፌሰር መስፍን መጽሀፍ “መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ” ን ይመለከታል …. እሱንም ማንበብ ለምትፈልጉ በpdf ብሎጋችን ላይ እናስቀምጥሎታለን፡፡
andadirgen.
No comments:
Post a Comment