Sunday, 10 March 2013

ያስፈራል፤ ግን ኢትዮጵያ አትፈርስም!…..(Pro/Mesfin Woldemariam)



mesfin-woldemariamይቺ ኢትዮጵያ የምትባል አገር ስንት የመከራ ወንዞችን ተሻግራለች! ገና ስንት ትሻገራለች! ስንት የግፍ ተራራዎችን አቋርጣለች! ገና ስንት ታቋርጣለች! ስንት የበደል ሰይፎችንና ጦሮችን አምክናለች! ገና ስንት ታመክናለች! ስንት የውጭ ኃይሎችን አሳፍራለች! ገና ስንቱን ታሳፍራለች! ስንት አምባገ- ነኖችን እያለቀሰች ቀብራለች! ገና ስንቱን ትቀብራለች! ጭቆና ከኢትዮጵያውያን ደም ሙልጭ ብሎ ወጥቶ በነፃነት፣ በእኩልነት፣ በዳኝነት በጠራ ደም እስቲተካ ድረስ ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ዘርግታ ትጸልያለች! እግዚአብሔርም ቃል ኪዳን አለበት ይሰማታል! የኃያላን ኃያል ኢትዮጵያ እንድትፈርስ አይፈቅድም!
የኢትዮጵያን መፈራረስ የሚመኙ ግለሰቦችም መንግሥቶችም ሞልተዋል፤ ኢትዮጵያ እንድትፈራርስ የሚመኙ ጭንጋፍ ልጆችም አሏት፤ ማኅጸንዋ እየደማ እየረገማቸው ሰላምና እንቅልፍ አጥተው አብጠው ይፈነዳሉ፤ የኢትዮጵያን መፈራረስ የሚመኙ መንግሥቶች ሁሉ ከዚህ በፊት ቀድመው ፈራርሰዋል፤ ወደፊትም ይፈራርሳሉ።
የአገራቸው ፍቅር፣ የእርስ በርሳቸው ዝምድና፣ የተራራውና የሸለቆው፣ የሜዳውና የገደሉ፣ የበረሀውና የለምለሙ፣ የዝናቡና የወንዙ፣ የዓየሩና የነፋሱ፣ የበዓላቱና የድግሱ፣ ያለውን አብሮ መቋደሱ፣ ተዝካሩ፣ ሙታ ዓመቱ ለሞቱ፣ መላእክቱ፣ ቅዱሳቱ፣ ሰማዕታቱ፣ እየተሸከሙ ያደረሱት ጸሎቱ፣ ለምዕተ-ዓመታት የተከማቸው እምነቱ፣ ሃይማኖቱ፣ በዚህ ሁሉ የተገነባው ኅብረቱ እንዴት ይፈርሳል! ማን ችሎ ያፈርሰዋል! አፍራሾች ቀድመው ይፈርሳሉ!
አንዳንዶች ቢጨነግፉም፣ አንዳንዶች ቢክዱም፣ አንዳንዶች ሆዳም ቢሆኑም፣ አንዳንዶች ቢወላውሉም፣ ኢትዮጵያ ልጆች አሏት፣ አሁንም የሚሞቱላት፣ ያልበሏት፣ የሚሳሱላት፤ ያልሸሿት፤ አፈሯን የሙጢኝ ብለው አፈርሽ እንሁን የሚሏት፣ ደሀነትም ሆነ ጭቆና ካንቺ አይለዩንም የሚሏት፣ ኢትዮጵያ ዛሬም ልጆች አሏት ስትፈርስ ቆመው የማያዩ፣ ሲያማት ነፍሳቸውን ዘልቆ የሚያማቸው፣ ሳልፈርስ አትፈርስም ነው ቃል ኪዳናቸው።
ቱርክና ግብጽ መጥተው ሄደዋል፤ ፖርቱጋል መጥቶ ሄዷል፤ እንግሊዝ መጥቶ ሄዷል፤ ኢጣልያ መጥቶ ሄዷል፤ ጠላቶች እየመጡ በመጡበት ተሸኝተዋል፤ ወዳጆች በጨዋነት ተስተናግደው ተዋኅደዋል፤ ቤተ ሙሴ፣ ቤተ ክርስቲያን፣ ቤተ እስልምና ኢትዮጵያዊ ሆነዋል፤ ዛሬ እንግዳ አይደሉም፤ ዛሬ ባዕድ አይደሉም፤ ኢትዮጵያ በፍቅር ለመጣ ፍቅር ነች፤ ምቹ ነች፤በጠብ ለመጣ እሾህ ነች፤ ትዋጋለች።
ኢትዮጵያ፣ ነቢዩ ኢሳይያስ ለአንቺ የተናገረው ይመስለኛል፤ ‹‹ብርሃንሽ መጥቶአልና፣ የእግዚአብሔርም ክብር ወጥቶልሻልና ተነሺ፤ አብሪ፤ እነሆ ጨለማ ምድርን ድቅድቅ ጨለማም አሕዛብን ይሸፍናል፤ ነገር ግን በአንቺ ላይ እግዚአብሔር ይወጣል፤ ክብሩም በአንቺ ላይ ይታያል፤አሕዛብም ወደ ብርሃንሽ፣ ነገሥታትም ወደ መውጫሽ ጸዳል ይመጣሉ።
ዓይኖችሽን አንስተሽ በዙሪያሽ ተመልከቺ፤ እነዚህ ሁሉ ተሰብስበው ወደአንቺ ይመጣሉ፤ ወንዶች ልጆችሽ ከሩቅ ይመጣሉ፤ ሴቶች ልጆችሽንም በጫንቃ ላይ ይሸከሙአቸዋል፤ በዚያን ጊዜ የባሕሩ በረከት ወደአንቺ ስለሚመለስ፣ የአሕዛብም ብልጥግና ወደአንቺ ስለሚመጣ አይተሽ ደስ ይልሻል፤ ልብሽም ይደነቃል፤ ይሰፋማል፤ የግመሎች ብዛት የምድያምና የጌፌር ግመሎች ይሸፍኑሻል፤ ሁሉ ከሳባ ይመጣሉ፤ ወርቅንና ዕጣንን ያመጣሉ፤ የእግዚአብሔርንም ምስጋና ያወራሉ፤ የቄዳር መንጎች ሁሉ ወደ አንቺ ይሰበሰባሉ፣ የነባዮትም አውራ በጎች ያገለግሉሻል፤ እኔን ደስ ሊያሰኙ በመሠዊያዬ ላይ ይወጣሉ፤ የክብሬንም ቤት አከብራለሁ።›› (60/1-7)
ኢትዮጵ ትወድቅ ይሆናል፤ ግን ያለጥርጥር ትነሣለች፤ በፊትም ወድቃ ተነሥታለችና፤ ኢትዮጵ ትሰነጠቅ ይሆናል፤ ግን ያለጥርጥር ትገጥማለች፤
በፊትም ተሰንጥቃ ገጥማለችና፤ ለኢትዮጵያ በጎ የማይመኙላት የአየሉ ቢመስሉም የንስሐ ጊዜ ስትሰጣቸው ነው፤ ኢትዮጵያ ዕብሪተኞችንም ትሕትና ታስተምራቸዋለች፤ ዕብሪተኞች ከነዕብሪታቸው በራሳቸው እሳት ቀልጠው እስቲያልቁ ኢትዮጵያ ትእግስትዋ አያልቅም፤ ኢትዮጵያ ትእግስት ነችና።
በበጎ መንፈስ እስከተመራን ድረስ፣ ፍርሃትንና አለመተማመንን፣ ጥላቻን፣ ጠብንና ድብድብን፣ ሊዘሩብን ከሚፈልጉ ርኩሳን መናፍስት ከራቅን ኢትዮጵያችን አትፈርስም፣ የደፈረሰውም ቶሎ ይጠራል።

No comments:

Post a Comment