Monday, 25 March 2013

የመለስ ዜናዊ ራዕይና መተካካት ያልተንጸባረቀበት የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ስብሰባ ተጠናቀቀ


የመለስ ዜናዊ ራዕይና መተካካት ያልተንጸባረቀበት የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ስብሰባ ተጠናቀቀ


News, Ginbot 7 Movement for Justice, Freedom and Democracy.

የመለስን ራዕይ ከግቡ ሳናደርስ እንቅልፍ አይወስደንም ብለዉ ሲዝቱ የከረሙት የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች “መተካካት” የሚለዉን ዋናዉን የመለስ ፖሊሲ ወደ ጎን ትተዉ ሰሞኑን በተከታታይ ባካሄዷቸው ስብሰባዎች በአብዛኛው ነባር አመራራቸዉን መርጠዉ ድህረ መለስ ጉዟቸዉን መጀመራቸዉን ዘጋቢዎቻችን ከአዲስ አበባ በላኩልን ዜና ገለጹ፡፡ በዚህ ባሳለፍዉ ሳምንት ዉስጥ አዋሳ፤ መቀሌ፤ አዳማና ባህርዳር ላይ በተካሄዱት የየፓርቲዉ ጉባኤዎች ላይ መለስ ዜናዊ መተካካት ብሎ የጀመረዉ ነባር የፓርቲ ሹማምንትን በአዲስ የመተካት ፖሊሰ እምብዛም በተግባር ባይዉልም አራቱም ድርጅቶች በተወሰነ ደረጃም ቢሆን አንዳንድ ነባር አባላቶቻቸዉን ከፓርቲዉ የስራ አስፈጻሚ ከሚቴ አስወግደዋቸዋል፤  በዚህም መሠረት ደአህዴን ተሾመ ቶጋን፤ ህወሀት ስዩም መስፍንን፤ብርሀኔ ገ/ክርስቶስንና አርከበ ዕቁባይን፤ኦህዴድ  አባዱላ ገመዳን፣ ግርማ ብሩንና ኩማ ደመቅሳን ብአዴን ደግሞ ብርሃን ኃይሉን ከስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነት አሰናብተዋቸዋል።
ሟቹ መለስ ዜናዊ በቀየሰዉ ዕቅድ መሰረት መተካካት እስከ 2007 ዓ.ም ድረስ ቀጥሎ ከ2007ቱ ምርጫ በሁዋላ ነባር የአመራር አባላት ሙሉ በሙሉ ይለቃሉ ተብሎ የተገመተ ቢሆንም በሰሞኑ የፓርቲዎች ስብሰባ እንደታየዉ ግን ነባር ታጋዮች ስልጣናቸዉን እንደያዙ እንዲቀጥሉ ተደርጓል። በ2003 ዓ.ም በተደረገዉ የመተካካት ሹምሽር የኃላፊነት ቦታዉን አጥቶ የነበዉ የብአዴኑ አዲሱ ለገሰ ተመልሶ ወደ ስልጣን የመጣ ሲሆን በቅርቡ በወጣት መሪዎች ይተካሉ ተብሎ ሲጠበቅ የነበረዉ በረከት ስምኦን፤ ህላዊ ዮሴፍና፣አባይ ወልዱ ጭራሽ ስልጣናቸውን እያጠናከሩ መምጣታቸዉ ታዉቋል።
በ2003 ዓም በተደረገዉ መተካካት የመንግስትና የፓርቲ ኃላፊነታቸውን የለቀቁት ስዩም መስፍንና ሌሎች ዘጠኝ የህወሃት አባላት ከጤና ጋር በተያያዘ በራሳቸው ፈቃድ  ድርጅቱን ለመልቀቅ ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት የተሰናበቱ ሲሆን የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ግን የእነዚህን ሰዎች መሰናበት ከመተካካት ጋር አያይዞ ዘግቧል። በአጠቃላይ ብዙ ዉጣዉረድና ድራማ የታየበት የዘንድሮዉ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ስብሰባ ሲጀመር የመለስ ዜናዉን ራዕይ ከግቡ እናደርሳለን በሚል መሪ ቃል የተጀመረ ሲሆን ሲፈጸም ግን በመርገጥ “መተካካት” የሚለዉን የድርጅቱን መስራች አላማና ራዕይ በሌላ ነገር በመተካት ተፈጽሟል።
ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት በአንድ ጊዜ መልቀቂያ ማቅረባቸው አጋጣሚ ሳይሆን ከመለስ ህልፈት በሓላ በህወሃት ውስጥ ከተፈጠረው ልዩነት ጋር በተያያዘ ሳይሆን እንደማይቀር ምንጫችን ቢጠቅስም ይህን በተመለከተ ለማረጋገጥ ያደረግነው ሙከራ ለጊዜው አልተሳካም፡፡ ብዙዎች እንደሚገምቱት ከአርከበ እቁባይ ጋር ጤነኛ ግንኙነት ያልነበራት  አዜብ መስፍን በዚህ ጉባኤ በድል አድራጊነት ወጥታለች።
ከፊታችን ቅዳሜ መጋቢት 14 ቀን እስከ 17 ቀን 2005 ዓ.ም በባህርዳር ከተማ የሚካሄደው የኢህአዴግ ጉባዔ ኃይለማርያም ደሳለኝን በሊቀመንበርነት፣ ደመቀ መኮንን በምክትል ሊቀመንበርነት በድጋሚ ይመርጣል ተብሎ እንደሚጠበቅ ምንጮቻችን ጠቁመዋል፡፡
የወያኔ ኢህአዴግ ድርጅቶች ያደረጉትን ሹም ሽር በተመለከተ ጥያቄ ያቀረብንላቸው አንድ የቀድሞ የሀወሀት ነባር ታጋይ ፡ ምርጫውን “ውሀ ቢወቅጡት ነው” ብለውታል። “ከእነዚህ ሰዎች ምንም የሚጠበቅ ነገር የለም፣ ምን አዲስ ነገር እንደማይፈጥሩም ይታወቃል። የአፈና ስርአቱ እንደሚቀጥል ጥሩ ማሳያ ነው” ብለዋል ታጋዩ።
http://www.ecadforum.com/Amharic/archives/6695

No comments:

Post a Comment